
የስኳር አካዳሚ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መስጠት ሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በምርምርና ስልጠና ዘርፍ የሚገኘው የስኳር አካዳሚ በቴክኒክና ሙያ ትህርት ስልጠና መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ፡፡
ወንጂ የሚገኘው አካዳሚ ከኢፌዴሪ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በዘርፉ በመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብር ስልጠና እንዲሰጥ ፈቃድ ያገኘው ነሐሴ 10 ቀን 2016ዓ.ም ነው፡፡
በተሰጠው ፈቃድ መሠረት የስኳር አካዳሚ በሹገር ማኑፋክቸሪንግ ፕሮሰሲንግ ከደረጃ 1 እስከ 4፣ በሹገር ኤንድ ኤታኖል ፕሮሰሲንግ ኳሊቲ ኮንትሮል ከደረጃ 2 እስከ 4፣ በስቲም ኤንድ ፓውር ጀኔሬሽን ኤንድ ዲስትሪቢዩሽን ከደረጃ 2 እስከ 4 በመደበኛው መርሐበግብር ስልጠና ይሰጣል፡፡
ፈቃዱ በሹገር ኬን ፕሮዳክሽን ከደረጃ 2 እስከ 4፣ በኢሪጌሽን ኤንድ ድሬይንኤጅ ከደረጃ 1 እስከ 4፣ በአግሪካልቸራል ማሽነሪስ ኤንድ ኢኪውፕመንት መካኒክስ ከደረጃ 1 እስከ 4፣ በአግሪካልቸራል ማሽነሪስ ኤንድ ኢኪውፕመንት ኦፕሬሽን ከደረጃ 1 እስከ 4 ስልጠና መስጠትም የሚያስችል ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ምስረታ ጋር ተያይዞ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ የተቋቋመው የስልጠና ማዕከል ላለፉት በርካታ ዓመታት ለነባር የኢንዱስትሪው ሰራተኞች አጫጭር እና አዲስ በተቋሙ ለሚቀጠሩ ባለሙያዎች የዘርፉን ማስተዋወቂያ ስልጠናዎችን (Induction) ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታትም የተቋሙን አቅም በማሳደግ እና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ለማግኘት እና መደበኛ ስልጠና ለመጀመር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአዲስ መልክ ከተቋቋመበት ከመጋቢት 2014ዓ.ም ጀምሮ አካዳሚው ዕውቅና አግኝቶ መደበኛ ስልጠና እንዲጀምር የሙያ ደረጃ (Occupational Standard) ፣ የማሰልጠኛ ስነ ዘዴ (Training Curriculum) እና የስልጠና ምዘና ሰነድ (Training Assessment Package) የክለሣ ሥራ በአካዳሚው እና በፌደራል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ተከናውኖ በሰባት የሙያ ዘርፎች ስልጠና መስጠት የሚያስችለው ፈቃድ እንዲገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡