
በአመራር ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና በስኳር አካዳሚው እየተሰጠ ነው
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአዲስ ተልዕኮ ከመቋቋሙ ጋር ተያይዞ እራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ ከተደረጉ ሶስት ስኳር ፋብሪካዎች ለተውጣጡ 36 ቡድን መሪዎች እና ሱፕርቫይዘሮች ከመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአመራር ክህሎት ዙሪያ ያጠነጠነ ስልጠና በግሩፑ የስኳር አካዳሚ እየተሰጠ ነው፡፡
በዚህ የስልጠና መርሐግብር ከፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ 18፤ ከመተሀራ ስኳር ፋብሪካ 10 እንዲሁም ከወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ 8 አመራሮች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን በዚህም የሶስቱ ስኳር ፋብሪካዎች አመራሮች ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ እያከናወናቸው የሚገኙትን የሌማት ትሩፋት ሥራዎች እንዲሁም የፋብሪካውን ለ2017 በጀት ዓመት የምርት ዘመን ዝግጅት የተመለከተ ተሞክሮ እንዲቀስሙ የአንድ ቀን የጉብኝት መርሀ-ግብር የተዘጋጀ መሆኑም ከአካዳሚው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
ይኼው ስልጠና የግሩፑ ስኳር አካዳሚ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እራሳቸውን ችለው ከወጡ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር በፈጸመው ስምምነት እና በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ስልጠና መሆኑን እና ፋብሪካዎቹ እራሳቸውን ችለው ከተቋቋሙ ወዲህ ቀደም ሲል በአካዳሚው ይሰጥ የነበረ መሰል አጫጭር ስልጠና ተቋርጦ የቆየበት ሁኔታ እንደነበር ከአካዳሚው የተገኘው መረጃ አክሎ ገልጿል፡፡
የግሩፑ ስኳር አካዳሚ በ2016 ዓ.ም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፈቃድ ባገኘባቸው የስልጠና መርሀ-ግብሮች መደበኛ ስልጠናዎችን በያዝነው ዓመት ለመጀመር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመቁረጫ ወይም የሰልጣኞች መግቢያ ነጥብ እየጠበቀ እንደሆነ እና በአካዳሚው በኩልም ከመሰል ተቋማት ልምድ የመቀመርና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡