• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
“የአገር ሀብት የሆነውን ፋብሪካ ውጤታማ ለማድረግ የጸጥታ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል”

“የአገር ሀብት የሆነውን ፋብሪካ ውጤታማ ለማድረግ የጸጥታ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል”

                             የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ

  • ከፎርማኖች፣ሱፐርቫይዘሮች እና ሲኒየር ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

ከፍተኛ መዕለ ንዋይ የፈሰሰበትንና የአገር ሀብት የሆነውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 እና 1 ስኳር ፋብሪካ የሚጠበቅበትን ምርት በተገቢው መልኩ እንዲያመርትና ውጤታማ እንዲሆን በአካባቢው ተሰማርተው የሚገኙ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ ከደቡብ ኦሞ እና ከምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ወረዳዎች ከተውጣጡ አመራሮችና የጸጥታ አካላት እና በስፍራው ከሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው ይህን የገለጹት፡፡

በውይይታቸው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 እና 1 ስኳር ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ መስራት እንዲችልና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች መሳብ እንዲችል ፋብሪካው በሚገኝበት አካባቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ጥቃቅን ችግሮች ተወግደው መረጋጋትና ሠላማዊ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ የፋብሪካው አመራር፣ ፋብሪካው የሚገኝባቸው የደቡብ ኦሞ እና የምዕራብ ኦሞ ዞኖች አመራሮች፣ በአካባቢው የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ አካለት ተቀናጅተው መስራትና እንዲሁም የተቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴን አጠናክሮ ወደሥራ ማስገባት አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ወዮ አመልክተዋል ፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው ከጸጥታ አካሉ ጋር ተባብሮ እና ተናብቦ የመስራት ልምድ የበለጠ ተጠናክሮ አንዲቀጥል በዞንና በወረዳ ደረጃ የተዋቀሩት ስትሪንግ ኮሚቴዎች የጋራ ዕቅድና የትግበራ ዕቅድ አዘጋጅተው በፍጥነት ወደሥራ መግባት እንዲሁም በጋራ የአፈጻጸም ግምገማ እያደረጉ መሥራት ይገባል ብለዋል ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡

በስብሰባው የተሳተፉ የደቡብ ኦሞ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አመራር አባላት ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰበትን ስኳር ፋብሪካ ውጤታማነት የበለጠ ለማሻሻል በቅንጅት ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትና ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፋብሪካው ፎርማኖች፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ሲኒየር ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

በፋብሪካው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው ውይይትም ቀጣዩን የፋብሪካውን የምርት ወቅት በስኬት ማጠናቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡

በዚሁ ውይይት ማጠናቀቂያ ላይ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በሰጡት ማጠቃለያ በልዩ ልዩ ደረጃዎች የሚገኙ ባለሙያዎችም ሆኑ ሠራተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊት በተገቢው መልኩ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ፋብሪካውን ወደፊት ሊወስደው ወይም ወደኋላ ሊጎትተው የሚችለው መካከለኛ አመራሩ ነው ያሉት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህንን በሚገባ መረዳትና ለለውጥ መነሳሳት ተገቢ መሆኑንም በማጠቃለያቸው አስገንዝበዋል፡፡

የፋብሪካው የሠራተኛ ማሕበርም ፋብሪካው ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡