• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ሠራተኛው የፋብሪካው ባለቤት ሆኖ መስራት እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

ሠራተኛው የፋብሪካው ባለቤት ሆኖ መስራት እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 እና 1 ስኳር ፋብሪካ አመራሮችና ሠራተኞች የስኳር ምርትን ለማሳደግ፣ የማምረቻ ወጪዎችን ለመቀነስና በዋናነት ብክነትን ለማስወገድ በባለቤትነት መንፈስ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ ግሩፑ ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 እና 1 ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ያዘጋጀውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የፋብሪካው የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች የስኳር ምርትን ለማሳደግ፣ የማምረቻ ወጪዎችን ለመቀነስና በዋናነት ብክነትን ለማስወገድ በትጋት መስራትና በባለቤትነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የሥራ መሪውም ሆነ ሠራተኛው ተጠቃሚ እና ጠቃሚ ለመሆን ፋብሪካው ያሉበትን የውስጥ ችግሮች በጋራና በባለቤትነት መንፈስ እንዲሁም በትጋት መስራት ሲቻል ብቻ መሆኑን ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በንግግራቸው አመልክተዋል፡፡

አያይዘውም ፋብሪካው በእጁ ያሉትን ዕድሎች ተጠቅሞ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን መለየትና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ሁሉም የሚጠበቅበትን አስተዋጽዖ ሳይቆጥብ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ለፋብሪካ መለወጥ መፍትሔ የሚመነጨው ከውስጥ ነው ያሉት ክቡር አቶ ወዮ ኦሞ 3 እና 1 ስኳር ፋብሪካም የሚገኝበትን ሁኔታ ገምግሞ መፍትሔ ማምጣት እንደሚችል እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡

የፋብሪካው ሠራተኞችና አመራሮች በትንሽ ጥረት በቀላሉ ሊለማና ሊበለጽግ የሚችል ሃብት በእጃቸው ያለ መሆኑን በመረዳት ቀጣዩን የኦፕሬሽን ጊዜ በስኬት ለማጠናቀቅ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የፋብሪካው የሥራ መሪዎች፣ ሠራተኞችና የሠራተኛ ማህበሩ ፋብሪካው ያለበትን ወሳኝና ታሪካዊ ምዕራፍ በመረዳት እጅ ለእጅ ተያይዘው ቀደምት አፈጻጸሞችን ለማካካስና ውጤታማ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ተስፋዬ በበኩላቸው ፋብሪካው ቀድሞ ከነበረበት ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ይመጣ ዘንድ የሥራ መሪዎችና ሰራተኛው ጠንክረውና ተናበው መስራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀድሞ የነበሩ ውጤታማ ያልሆኑ አሰራረሮችን ለማሻሻልና ውጤታማነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዳዲስ ለውጦችን ለመቀበል እንዲሁም የባለቤትነትና የቡድን መንፈስን  የሥራ ባህል  በማድረግ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡