
ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
- ከፋብሪካው ፎርማኖች፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ሲኒየር ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ለዋና መስሪያ ቤት እና ፋብሪካዎች አመራሮችና ሠራተኞች በተከታታይ በመስጠት ላይ የሚገኘው የአቅም ግንባታ ስልጠና ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም በፋብሪካው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች በፋብሪካው ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀምና ምርታማ ለመሆን በቡድን መንፈስ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
የፋብሪካው ሠራተኛ ፋብሪካው ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ በተገቢው መልኩ መረዳትና ነባራዊ ሁኔታዎችን የበለጠ ለማስተካከል ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ሠራተኛው አዎንታዊ የቡድን መንፈስ ገንብቶ የፋብሪካውን ግቦችና ተልዕኮ ለማሳካት መስራት እንዳለበትም ነው ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት፡፡
ፋብሪካው በራሱ የገቢ ድርሻ ብቻ የሚተዳደር መሆኑን ሠራተኛው ተገንዝቦ የተጀመረውንና ወደሥራ የገባውን ለውጥ በማፋጠን ረገድ ቁርጠኛ በመሆን በዕውቀቱ እና በጉልበቱ እገዛ ማድረግ እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው ፋብሪካው ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት ይችል ዘንድ ቡድናዊ መንፈስ ተላብሶ ለአንድ ግብ መሰለፍና ለውጤት መብቃት ከፋብሪካው አመራሮችና ከሰራተኛው ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ስልጠናው በግሩፑ የኮርፖሬት ጉዳዮች ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመድኩን ተክሌ እና የዕቅድ፣ ልማትና ስጋት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ዮሴፍ በጋሻው አማካይነት ነው የተሰጠው፡፡
በተያየያዘ ዜና ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በፋብሪካው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከፋብሪካው ፎርማኖች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ሲኒየር ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም ቀጣዩን የፋብሪካውን ኦፕሬሽን በስኬት ማጠናቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡
በዚሁ ውይይት ላይ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በሰጡት ማጠቃለያ ፎርማኖች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ሲኒየር ባለሙያዎች ሠራተኛው በተሰማራበት መስክ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ኃላፊነታቸውን በተገቢው ደረጃ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ፋብሪካውን ውጤታማ ሊያደርገው አሊያም ግቡን እንዳያሳካ ሊያደርገው የሚችለው መካከለኛ አመራሩ ነው ያሉት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህንን በሚገባ መረዳትና በቡድን መንፈስ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡


