የግሩፑ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች “የህልም ጉልበት ለዕምርታዊ ዕድገት” በሚል ርዕስ ውይይት አካሄዱ
ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች “የህልም ጉልበት ለዕምርታዊ ዕድገት” በሚል ርዕስ ለፌዴራል የመንግስት ተቋማት ሠራተኞች በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ማክሰኞ ህዳር 10 ቀን 2017ዓ.ም በአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ውይይቱን የመሩትና የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት በግሩፑ የማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታፈሰ አሰፋ ባደረጉት ገለጻ፤ ውይይቱ ወቅታዊ፣ የመንግሥት ሠራተኛው መንግስት ምን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ግንዛቤ የሚያገኝበት፣ በቀጣይ ምን እንደሚጠበቅበት የሚገነዘብበትና መንግሥት ከሠራተኛውና ህዝብ ምን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ለውይይቱ የቀረበው ሰነድ ከሰባ ዓመታት ጀምሮ የነበሩ ሀገራዊ የፖሊቲካ ሁኔታዎች እና እነዚህን ሁኔታዎች ተከትሎ የመጣው ለውጥ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድና ከአፍሪካ አንጻር ያላትን የኢኮኖሚና የዲፖሎማሲያዊ ተጽዕኖና ቀጣይ ተስፋ፣ ያላት የመልማት አቅም ምን እንደሚመስል በዝርዝር ቀርቧል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ አመሠራረት፣ ፓርቲው አሁን የሚገኝበት ሁኔታ በዚህ ውስጥ ለፓርቲው መመስረት አስፈላጊ የሆኑ ምክንያቶችንም ዘርዝረዋል፡፡
አክለውም የብልጽግና ፓርቲ ትሩፋቶችና ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በስፋት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ተቀባይነት ያለው ሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ስለወል ትርክት ምንነት፣ የወል ትርክት ግንባታና አስፈላጊነትን በተመለከተ፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ስለተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዘርዝረዋል፡፡
በማጠቃለያቸውም ሠራተኛው ለግልና የጋራ ህልሞች መሳካት መሰናክሎችንና ጎታች ግፊቶችን የሚሻገር፣ ከፍ ያለ ትጋትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ መላበስ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ የመንግስት ሠራተኛው ቁልፍ ኃላፊነት መሆኑንም አቶ ታፈሰ አስገንዝበዋል፡፡
ሰነዱ ከቀረበ በኋላ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ያቀረቡ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡