
በኦሞ ቤልት ስኳር ፋብሪካዎች የ2017 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ላይ ውይይት በመደረግ ላይ ነው
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በኦሞ ቤልት በሚገኙት የኦሞ ቁጥር 2 እና ቁጥር 3/1 ስኳር ፋብሪካዎች የ2017 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት በመደረግ ላይ ነው፡፡
በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ግምገማና የስልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በ2017 በጀት ዓመት ፋብሪካዎቹ ያጋጠሟቸውን ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በመቋቋም ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት የአመራር እንዲሁም በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ እና በባለቤትነት ስሜት በርብርብ መስራት ከተቻለ ኢንዱስትሪውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሻለ መልኩ ውጤታማ ማድረግ አዳጋች እንደማይሆን ማሳያ ነው ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
የተያዙ ዕቅዶችን በመሳካት ረገድ የሚስተዋሉ አብዛኛዎቹ ተግዳሮቶች የአመራር አቅምን በማሳደግ እና የቡድን መንፈስን በማጎልበት ሊወገዱ የሚችሉ መሆናቸውን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የስልጠና መድረክ እና ከተደረገው ውይይት መገንዘብ መቻሉን ያስታወሱት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በወቅቱ የተለዩትንና ሊቀረፉ የሚችሉት ችግሮች ለመቅረፍ ምን ያህል ጥረት አድርገናል የሚለውን በአግባቡ መፈተሸ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በየዕቅድ አፈጻጸማችን የሚሻሻሉ ችግሮች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች በተፈቱበት መጠን እና ፍጥነት የሚለኩ መሆኑንም መዘንጋት እንደማይገባ ክቡር አቶ ወዮ አስታወሰዋል፡፡
የ2018 የስኳር ምርት ዕቅድን ለማሳካት የፋብሪካዎቹ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በጽኑ የባለቤትነት ስሜት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተያያዘም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ ቶማ የፋብሪካውን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ከግሩፑ የመጣው የኢንስፔክሽን ቡድንም በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ተገኝቶ ያደረገውን ግምገማ ሪፖርት የግሩፑ የትራንስፎርሜሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ሳምሶን ወልቀባ አማካይነት ቀርቧል፡፡
የፋብሪካዎቹ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በሦስት ምድቦች ማለትም በእርሻ፣ በፋብሪካና በድጋፍ ሰጪ ክፍሎች ተመድበው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡



