ብሔራዊ የምርምር ስራዎች ግምገማ ተካሄደ
በኢትየጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ አገር ዓቀፍ የምርምር ስራዎች ግምገማ መድረክ ተካሄደ።
በዚህ ከህዳር 8 እስከ ህዳር 11 ቀን 2018ዓ.ም በወንጂ በተካሄደው የምርምር ስራዎች ግምገማ መድረክ ላይ ሰባት የምርምር ውጤቶች (ግኝቶች) እና 17 የምርምር ፕሮፖዛሎች ቀርበውና ውይይት ተደርጎባቸው ጸድቀዋል።
ሰባቱ የምርምር ግኝቶች (ውጤቶች) በዝርያ ማሻሻል፣ በእርሻ ምህንድስና እና በአፈር ሳይንስ እንዲሁም በስኳር ቴክኖሎጂ እና ምሕንድና ዘርፎች የተከናወኑ ናቸው።
የምርምር ፕሮፖዛሎቹ ደግሞ በአምስት ዘርፎች ማለትም በዝርያ ማሻሻል፣ በእርሻ ምህንድስና እና በአፈር ሳይንስ፣ በስኳር ቴክኖሎጂ እና ምሕንድስና፣ በሰብል አመራረትና ጥበቃ እንዲሁም ማሕበረ ምጣኔ ሀብትን ትኩረት አድርገው ምርምር የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው።
በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አመልክተው በዚህ ተልዕኮ ውስጥ የዘርፉ ተመራማሪዎች ሚናቸውን ለመወጣት በንቃት መሳተፍና አሻራቸውን ማኖር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የዘርፉ ተመራማሪዎች በዚህ የአገር የለውጥ ሂደት ውስጥ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግና አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እንዲሁም ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ በምርምር እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ መደገፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ስኳር ፋብሪካዎች ወደሙሉ የማምርት አቅማቸው እንዲደርሱና እንዲያመርቱ ምርምር የመሪነት ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ የቀረቡት የምርምር ውጤቶችና ወደ ፋብሪካዎች በፍጥነት ወርደው ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸውና ምርምር ሊደረግባቸው የጸደቁ ፕሮፖዛሎችም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርምር እንዲደረግባቸው ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በዓመታዊ የምርምር ስራዎች ግምገማ መድረክ ላይ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ ከልዩ ልዩ የግብርና ምርምር ማዕከሎች የተውጣጡ ከፍተኛ ተመራማሪዎች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም የግሩፑ የስራ መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።