• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ዓመታዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ በስኳር አካዳሚ ተካሄደ

ዓመታዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ በስኳር አካዳሚ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ዓመታዊውን የምርምር ግምገማ ወንጂ በሚገኘው በስኳር አካዳሚ አዳራሽ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 7 ቀን 2016ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በግምገማው ላይ 37 ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች በልዩ ልዩ ጠንካራ የግምገማ ሂደቶች ያለፉ የምርምር ውጤቶችና የምርምር መነሻ ሐሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተካሄደው ግምገማ በአምስት የተለያዩ የምርምር ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩና በፕሮግራም ደረጃ በሁለት የተለያዩ ገምጋሚዎች የተገመገሙ 35 የምርምር መነሻ ጽሑፎችና የምርምር ውጤቶች ቀርበዋል፡፡

የምርምር ስራዎቹ በፕሮግራም ደረጃ የተደረገውን የግምገማ ሂደት ያለፉ ሲሆን በመድረኩ ቀደም ብሎ በተመደቡ ወሳኝ ገምጋሚዎች (Critical Reviewers) እና በታዳሚዎች ጥብቅ ግምገማ ተደርጎባቸዋል። በመድረኩም ከሁሉም የስኳር ፋብሪካዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል።

በተለያዩ ስኳር ፋብሪካዎች በሸንኮራ አገዳ ምርትና በስኳር ምርት ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍን ታሳቢ አድርገው በግምገማው ላይ ከቀረቡት 35 ጽሑፎች ስምንቱ የምርምር ውጤቶች ሲሆኑ አምስቱ ደግሞ ምክር አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ከቀሪዎቹ መካከል 15ቱ የምርምር ሐሳቦች፣ ስድስቱ የሂደት ሪፖርቶች ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የምርምር ጽሑፍ ዳሰሳ ነው፡፡

ገምጋሚዎቹ የቀረቡትን የጥናት ውጤቶችና ጽሑፎች በተገቢው መልኩ እንዲገመግሙና ገንቢ ግብረ መልሶቻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል በቂ የግምገማ ጊዜ እንደተሰጣቸውም ታውቋል፡፡

በመጨረሻም በምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር አወያይነት በግምገማው ሂደትና በአጠቃላይ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣይ መደረግ የሚገባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ የማጠቃለያ ውይይት መደረጉን የግሩፑ የምርምርና ስልጠና ማዕከል አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *