
በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ተቀጥረው ከሚሰሩ የሱርማ ማሕበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ተካሄደ
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ተቀጥረው በመስራት ላይ ከሚገኙ የሱርማ ማሕበረሰብ አባላት ጋር ጥቅምት 19 ቀን 2017ዓ.ም የአካባቢውን ጸጥታና ደህንነት በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1/3 ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳ ተስፋዬ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አመራር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ባደረጉት ንግግር ፋብሪካው የሚያከናውነውን የልማት ሥራ በአግባቡ ማከናወን እንዲቻል የአካባቢ ጸጥታና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የማህበረሰቡ ሚና የላቀ ነው ብለዋል፡፡
በፋብሪካው ተቀጥረው በመስራት ላይ የሚገኙ የማህበረሰቡ አባላት ለፋብሪካው ሠላምና ጸጥታ መጠበቅ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ፋብሪካው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጂነር ካሳ ጠቁመው በአርብቶ አደሩ ስም የሚነግዱ ወንጀለኞችን ማጋለጥና ለሕግ አሳልፎ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የፋብሪካው ሠራተኛ የሆኑ የማህበረሰቡ አባላት በበኩላቸው የአካባቢው ደህንነትና ጸጥታ እንዲጠበቅ የመረጃ ልውውጣቸውን በማጠናከር እና ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት ከፋብሪካው ጋር በጋራ እንዲሚሰሩ መግለጻቸውን የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡
