• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
የኦሞ ቤልትን እምቅ ዓቅም አሟጦ ለመጠቀም መስራት ይገባል ተባለ

የኦሞ ቤልትን እምቅ ዓቅም አሟጦ ለመጠቀም መስራት ይገባል ተባለ

ለስኳር ንዑሥ ዘርፍ ልማት በመከናወን ላይ የሚገኙ በርካታ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው በኦሞ ቤልት ያለውን የመልማት እምቅ ዓቅም አሟጦ ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የማክሮ ኢኮኖሚ ልዩ አማካሪ እና የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለጹ፡፡
በክቡር አምባሳደሩ የተመራና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የግሩፑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የተካተቱበት የልዑካን ቡድን በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፣ ከሥራ መሪዎችና ከሠራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ክቡር አምባሳደር ግርማ ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካዎች የሥራ መሪዎች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት የኦሞ ቤልት ሰፊ ለም መሬትና የውሃ ሀብት ያለው በመሆኑ ይህንን ዕምቅ ዓቅም በማልማት አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከስኳር ንዑስ ዘርፍ ልማት በተጨማሪ የመንግስትንና የግሉን ዘርፍ ባሳተፈ መልኩ አካባቢውን የግብርና ልማት ማዕከል ለማድረግ እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡
ለስኳር ልማት ታስበው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ወስደው በመስራት ሥራዎቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ክቡር አምባሳደሩ አሳስበዋል።