
ስኳር አካዳሚ መደበኛ ስልጠና መስጠት ጀመረ
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ስኳር አካዳሚ ፈቃድ ካገኘባቸው የስልጠና ዘርፎች በአራቱ መደበኛ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ የአካዳሚው የመደበኛ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአካዳሚው መሰብሰቢያ አዳራሽ መጋቢት 29 ቀን 2017ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት በግሩፑ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈታሚ አቶ አባይነህ ባዘዘው ባደረጉት የመግቢያ ንግግር የሰው ኃይል ሁለንተናዊ ብቃት ለምርትና ምርታማነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው አካዳሚው መደበኛ ስልጠና መጀመሩ ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ በአጠቃላይና በተለይም ለምርምርና ስልጠና ዘርፍ ታሪካዊ ጅምር ነው ብለዋል፡፡
የስኳር የኢንዱስትሪውን ስፋትና ውስብስብነት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር ተያይዞ በዘርፉ ብቃት ያለው ባለሙያ ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህንን ክፍተት ለመሙላት አካዳሚው ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
የዘርፉ የሰው ኃይል ቀጣይነት ባለው መልኩ በንድፈ ኃሳብና በተግባር ተኮር ስልጠናዎች በመደገፍ ለተሰጠው ተልዕኮ ብቃቱ እየተረጋገጠ መሄድ እንደሚኖርበት የጠቆሙት አቶ አባይነህ የስኳር አካዳሚ ዕውቅና ባገኘባቸው እና ወደፊትም በሚያገኝባቸው የስልጠና ዘርፎች ይህንን ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መደበኛ ልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የስኳር አካዳሚ ዘርፉ ባለፈባቸው ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች በርካታ የስልጠና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን መስራቱን አስታውሰዋል።
ግሩፑ ኢንዱስትሪውን እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዋነኛው የሰው ሀብቱ ላይ መስራት ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት ለመደበኛ የስልጠና መርሐ ግብር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አስታውሰዋል። ለዚህም አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ የሙያ ደረጃዎችን፣ ሥርዓተ ሥልጠና እና የማሠልጠኛ መሳሪያዎች በማሟላት በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንዲጸድቁ ተደርገዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር አካዳሚ ከኢፌዲሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጠን በሰባት የሙያ ዘርፎች መደበኛ ሥልጠና መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱን የጠቆሙት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚሁ መሠረት በሸንኮራ አገዳ አመራረት፣ በመስኖና በስኳር አመራረት እንዲሁም በእንፋሎትና በኃይል ማመንጨት ዘርፎች ከደረጃ ሁለት ጀምሮ መደበኛ ሥልጠና መጀመሩ ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ፈቃድ በተገኘባቸው መስኮችም ስልጠናው የሚቀጥል መሆኑንም አስረድተዋል።
ከመደበኛው ሥልጠናው ጎን ለጎን ከዚህ በፊት በአካዳሚው ይሰጡ ለነበሩ አጫጭር ሥልጠናዎች የተዘጋጁ የብቃት አሃዶችን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ መሆናቸውንም ክቡር አቶ ወዮ አስታውቀዋል፡፡
አካዳሚው የስልጠና ጥራትን በማስጠበቅ፣ ሰልጣኞች በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት የታነጹ እንዲሁም የኢንዱስትሪውን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ እንዲሆኑ ከሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል፡፡
የስኳር አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ አመኑ አሰፋ በበኩላቸው አካዳሚው እስካሁን ያለፈባቸውን እና ወደፊት የሚጠበቅበትን ተግባራት በመርሐ ግብሩ ላይ አቅርበዋል። በዚሁ ወቅት አካዳሚው በመጪው መስከረም 2018ዓ.ም መደበኛ ስልጠና የሚሰጥባቸውን መስኮች በሁለት በመጨመር በስድስት መስኮች መደበኛ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በጠቅላላ ሜካኒክስና በሥራ አመራር መስኮች የሥልጠና ፈቃድ ለማግኘት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በይፋዊ የመደበኛ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ የሥራ መሪዎች እንዲሁም ከስኳር ፋብሪካዎች የተወከሉ ኃላፊዎችና የመጀመሪያ ዙር መደበኛ ሰልጣኞች የተገኙ ሲሆን የክብር እንግዶቹ የሥልጠና ክፍሎችን፣ ቤተ መጻሕፍቱን እና ተያያዥ አገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።