
የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካን ወደሥራ ለማስገባት በአገዳ ልማት ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
- አዲስ የተመደቡት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሠራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገዋል
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ተግዳሮቶች ስኳር ማምረት ያቆመውን የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካን ወደ ምርት ሥራው መልሶ ለማስገባት የፋብሪካውን የአገዳ ሽፋን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዲንሳ አብደና የተመራ ቡድን ሰሞኑን በፋብሪካው በመከናወን ላይ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተግባራትን ተዘዋውሮ በጎበኘትና ከሠራተኞች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት አርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካን በ2018 ዓ.ም. ወደ መደበኛ የምርት ሥራው መልሶ ለማስገባት በሸንኮራ አገዳ ተከላና ክብካቤ ረገድ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ከፋብሪካው ሠራተኞች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የግሩፑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዲንሳ አብደና እንደገለጹት ፋብሪካው ልዩ ልዩ ፈታኝ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ቢያሳልፍም ፋብሪካውን መልሶ ወደመደበኛ ምርት ሥራው ማስገባት አስፈላጊ በመሆኑ በሸንኮራ አገዳ ልማት ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን ማስፋት ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ተከላ የሚከናወነው በክረምት ወራት ብቻ የነበረ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህ በጀት ዓመት በፋብሪካው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሉትን የመስኖ ፓምፖች ሥራ በማስጀመር በበጋ ወራት የሸንኮራ አገዳ ተከላ እንቅስቃሴ መኖሩ አበረታችና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ይህንን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል እና በክረምት ወራትም የአገዳ ተከላና እና የእንክብካቤ ሥራውን በማስፋት አሁን በሸንኮራ አገዳ የተሸፈነውን የ1206 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ሽፋን ማሳደግ እና በ2018 ዓ.ም ፋብሪካውን ወደ መደበኛ ምርት ሥራው ለማስገባት ሠራተኛው እንደወትሮው ርብርብ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል አቶ ዲንሳ።
ከአገዳ ልማት ሥራው ጎን ለጎን በሰብል ምርት፣ ማንጎና ሙዝ እንዲሁም ንብ ማነብ የመሳሰሉ ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች በማስፋት ዶሮ እርባታና ከብት ማድለብን የመሳሰሉ ሥራዎችን መመልከት እንደሚገባም ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተደርገው የተመደቡት አቶ ሙሉጌታ ፋንታሁን የሥራ ርክክብና ከሠራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሥራ ርክክብና በትውውቁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሠራተኞችን በማስተባበር ፋብሪካውን በ2018 ዓ.ም ወደምርት ሥራው ለማስገባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካውን ወደ ምርት ሥራው የማስገባቱን ተግባር ዕውን ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደተጠበቀ ሆኖ የፋብሪካው ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ለጊዜያዊ ተግዳሮቶች ሳይበገሩ በአገዳ ተከላና ክብካቤ እንዲሁም ሌሎች የተጓዳኝ ልማት ተግባራት ላይ ያሳዩትን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።