
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነትናሉዓላዊነት በሚል ርዕስውይይት ተካሄደ
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አመራር አባላትና ሰራተኞች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት በሚል የመወያያ ርዕስ ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት አካሄዷል፡፡
ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የአዲስ አበባ መስተዳድር ፍትህ ቢሮ መሰብሰቢያ አዳራሽ የቀረበው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት በሚል እንደ ሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ግሩፑ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባይነህ ባዘዘው ሲሆኑ ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ በቤተሰብ ደረጃ በዘላቂነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ሀገራችንን የአደጋ ስጋት አይበገሬነት አቅም ለመፍጠር በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን፣ የእርዳታና ተረጂነት መዘዞችን እንዲሁም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ለብዙ አመታት የተረጂነት አስተሳሰብ ፈተና ሆኖባት መቆየቷና እያንዳንዱ ዜጋ በቀረበው ርዕስ ዙሪያ መግባባት ላይ መድረስና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት በተለይም ያሉንን የመሬት፣ የሰው ሀይል፣ የማእድንና የውሃ ሀብቶቻችን በአግባቡ ባለመጠቀማችን ምክንያት ለረጅም አመታት ከተረጂነት መላቀቅ አለመቻላችን የምያስቆጭ በመሆኑ ያሉንን እምቅ ሀብቶቻችን በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት መንፈስ በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር መውጣት እንዳለበትና ሁሉም በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አንስቷል።
በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳቦችና አስተያየቶች ማብራሪያ የሰጡት የኮርፖሬት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ እና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሳ ፍቃዱ የተነሱት ሀሳቦችና አስተያየቶች ገንቢ መሆናቸውን በመግለጽ በተለይ እንደ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሠራተኛ ለዚህ ሀገራዊ ራዕይ መሳካት መደረግ ያለበትን አበርክቶ አመልክቷል።
በመጨረሻም የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባይነህ ባዘዘው የአደጋ ስጋት አይበገሬነት ለመፍጠር እና ስራዎቻችን ይበልጥ ለማጠናከር የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ የአብሮነት እሴቶቻችን ይበልጥ ማዳበርና በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች ሀገራዊ ተግባራቶቻችን ያሳየነው ውጤት በቀጣይም በታቀዱ የልማት ስራዎቻችን ላይ አጠናክረን በማስቀጠል ተረጂነትን በአስተሳሰብም ሆን በድርጊት መቅረፍ እንደምገባ በመግለጽ የዕለቱ ውይይት ተጠናቋል፡፡