
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ተጀመረ
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ዕድሎችና ፈተናዎችን በአግባቡ በመገንዘብ በላቀ የአመራር ብቃትና የቡድን መንፈስ በመስራት ውጤታማ ተቋም መገንባትን ዓላማው ያደረገ የግሩፑ የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀምሯል፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ ስልጠናው ተቋሙ ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በጥልቀት ለመፈተሸና መፍትሔ ለማበጀት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የስልጠና መድረኩ ከፍተኛ አመራሩ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ቀረብ ብሎ ያላያቸው ጉዳዮች ካሉ ለማየትና የጎደሉ ነገሮች ካሉም ለመሙላት ዕድል እንደሚፈጥር ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
በስልጠናው የሚቀርቡ ርዕሰ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ አመራሩ የሚያደርገው ውይይት ወደራሱ እንዲመለከትና ያለበትን ሁኔታ ተረድቶ ለለውጥ እንዲነሳሳ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል ብለዋል ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትንሽ ጥረት ከተደረገበት ብዙ ሀብት ማፍራት የሚቻልበት ኢንዱስትሪ መሆኑን ያስታወሱት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዘርፉ ለአገር ተጨማሪ ሀብት እንዲፈጥር በርብርብ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
የ2017 የተቋሙን ዕቅድ ቢቻል ከዕቅድ በላይ ካልሆነ ግን የታቀደውን ያህል መፈጸም ለተቋሙ ወሳኝ መሆኑንም ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል፡፡
ክቡር አቶ ወዮ ሮባ ”የለውጥ ዕድል የማያባክን ውጤታማ ተቋም መገንባት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ የተለዩ ችግሮችን ለማረምና የማይቀለበስ ለውጥ ለማምጣት የተግባር ዕቅድ እንደሚዘጋጅም ይጠበቃል፡፡