
ለግሩፑ መካከለኛ አመራር አባላት የዓቅም ግንባታ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው
ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መካከለኛ አመራር አባላት አራት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
የስልጠና ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸውም ከዛሬ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆየው ይሄው የአቅም ገንባታ ስልጠና የተቋሙን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አያይዘውም ተቋሙ ባለፉት አምስት ዓመታት ሰፋፊ የሪፎርም ተግባራትን በማከናወን ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን አውሰተው በሪፎርም ሥራዎቻችን ያስመዘገብናቸው አበረታች ውጤቶች ከፍ ላሉ የሪፎርም ተግባራት የሚያንደረድሩን እንጂ የመጨረሻ ግቦቻችን አልነበሩም ብለዋል፡፡ አክለውም የሪፎርም ሥራ በተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው፣ቀለል ካሉ ተግባራት ጀምሮ ከባድና ውስብስብ ወደሆኑት አየተሸጋገረ የሚሄድ መሆኑን በመጠቆም ሀገርና ሕዝብ ከእኛ ወደሚፈልጉት ፤ እኛም አልመን ወደተነሳንበት ወሳኝ የሪፎርም ምዕራፍ ተሸጋግረናል ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በስልጠና መክፈቻ ንግግራቸው ማጠናቀቂያም የስልጠናው ተሳታፊ የመካከለኛ አመራር አባላት ተቋሙን ለስኬት ለማብቃት የአመራር ኃላፊነታችሁን በብቃት መወጣት ይኖርባችኋል፣ ለ2017 በጀት ዓመት ግሩፑ ከያዘው ዕቅድ በላይ ለማከናወን አሊያም ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ርብርብ ማድረግም ይጠበቅባችኋል በማለት በእርሳቸው በኩል “የለውጥ እድልን የማያባክን ተቋም መገንባት” በሚል ያዘጋጁትን የስልጠና ሰነድ አቅርበው የስልጠና ፕሮግራሙን አስጀምረዋል፡፡





