
በስኳር ፋብሪካዎች በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የክልሉን ወጣቶች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
በኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች በሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት በአርባ ምንጭ ከተማ ጥቅምት 29 ቀን 2017ዓ.ም ተካሄደ፡፡
በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያረጉት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለትና ሶስት ስኳር ፋብሪካዎች አካባቢን ለማልማትና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መገንባታቸውን አብራርተዋል።
ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ሰአት 11 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የጠቆሙት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቀጣይ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ 35ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጰያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የስራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው ደቡብ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ሊለማ የሚችል መሬት፣ ውሃ እና የሰው ሀይል ያለው ክልል መሆኑን በውይይቱ ላይ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ለክልሉ ትልቅ ፀጋ እና ዕድል መሆናቸውን የገፈለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም አብራርተዋል።
የስኳር ፋብሪካዎች ለወጣቱ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት፣ የፋብሪካውን ውጤታማት ማሳደግ እና የአካባቢውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የስራ ስምሪት አገልግሎት ማሻሻያ እና የሰራተኛ ምልመላና አስተዳደር ስራዎችን በተመለከተ ሰነድ ቀርቧል፡፡



