
በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3/1 ስኳር ፋብሪካ ዋና ከተማ የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ቦኖዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3/1 ስኳር ፋብሪካ ዋና ከተማ የነበረውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተገነቡ አምስት የመጠጥ ውሃ ቦኖዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ፡፡
የመጠጥ ውሃ ቦኖዎቹ ታህሳስ 18 ቀን 2017ዓ.ም በፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈይሳ ፈቃዱ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ የሥራ ክፍል ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡
ቦኖዎቹ ለአገልግሎት ክፍት ሲደረጉ ንግግር ያደረጉት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈይሳ ፈቃዱ የውሃ መስመሩ ለአገልግሎት መብቃቱ ቀደም ሲል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይመልሳል ብለዋል፡፡
የመጠጥ ውሃውን ቤት ለቤት ለማዳረስ የመስመር ዝርጋታ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት በራስ አቅም እንደሚከናወን የፋብሪካው የፕሮጀክት፣ መስኖና ሲቪል ሥራዎች ክትትል መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ኤና በበኩላቸው ገልጸዋል፡፡
ለጉድጓድ ቁፋሮ፣ በሰከንድ 8 ሊትር በሚገፋ ፓምፕ ከጉድጓድ የወጣው ውሃ ለሚጠራቀምበት ማጠራቀሚያ ግንባታና ከማጠራቀሚያ ወደ ቦኖዎቹ ለማገናኘት እንዲሁም ለፓይፕ ዝርጋታ፣ ለመንገድ ማቋረጫ ስትራክቸሮች ግንባታ፣ ለጄኔሬተር ቤት እንዲሁም ለቦኖ ግንባታ ስራ በአጠቃላይ ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡
ባይጌት ኮንስትራክሽን፣ ደቡብ ውሃ ሥራዎች እንዲሁም ንዑድ ኮንስትራክሽን የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በተለያዩ ሥራዎች መሳተፋቸው ተመልክቷል፡፡