
ግሩፑ የስኳር ኢንዱስትሪውን ወደላቀ ደረጃ የማሻገር ማዕከላዊ ሚናውን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል
- በግሩፑ የስድስት ወራት አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል
___________________________________________________________________
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ የማሻገር ማዕከላዊ ሚናውን በመወጣት ረገድ እያከናወነው የሚገኘውን ተግባር የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስታወቀ፡፡ በግሩፑ የስድስት ወራት አፈጻጸም ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኬሚካል ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር ወ/ሮ አስማ ረዲ የካቲት 13 ቀን 2017ዓ.ም በግሩፑ ዋና መስሪያ ቤት የግሩፑ የስድስት ወራት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ግሩፑ የአገሪቱን የስኳር ዘርፍ ወደላቀ ደረጃ ለማሻገርና ውጤታማ ለማድረግ አስካሁን ያደረገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ግሩፑ ሁሉንም ስኳር ፋብሪካዎችን ውጤታማ ማድረግ እና በአጠቃላይም ኢንዱስትሪውን ወደላቀ ደረጃ የማሻገር ሚናውን መወጣት በሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡
ግሩፑ በዘርፉ ቴክኒካልና ኦፕሬሽናል ዘርፎች ላይ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ አትኩሮ መስራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የፋብሪካ የሥራ መሪዎችን በማፍራት ረገድም ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል፡፡
የግሩፑን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የዕቅድ፣ ልማትና ስጋት አስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው በግማሽ ዓመቱ በግሩፑ ሥር በሚገኙት ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3 ስኳር ፋብሪካዎች የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡
በሁለቱ ስኳር ፋብሪካዎች በግማሽ ዓመቱ የተመረተው ስኳር በ2015ም እንዲሁም በ2016ዓ.ም በሙሉ ዓመት ከተመረተው የበለጠ መሆኑን በአብነት አንስተው ይህም የሚበረታታ አፈጻጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቀሪው ግማሽ ዓመትም የዋና ዋና ሥራዎች አፈጻጸም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ እንደሚሆን አመልክተው በሁለቱ ስኳር ፋብሪካዎች በአጠቃላይ ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር በምርት ዘመኑ እንደሚመረት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካዎች ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በዓመት ሁለት የምርት ወቅቶች እንዳላቸው ይታወሳል፡፡
የግምገማው ተሳታፊዎች ከግምገማው መጠናቀቅ በኋላ ግሩፑ በማስገንባት ላይ የሚገኘውን የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ጎብኝተዋል፡፡