• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ኢትዮጵያና ኩባ በስኳር ልማት ዘርፍ በጋራ ሊሰሩባቸው በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

ኢትዮጵያና ኩባ በስኳር ልማት ዘርፍ በጋራ ሊሰሩባቸው በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

  • የኩባ ስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ የባለሙያዎች ቡድን

            ያዘጋጀው የቴክኒካል ሰነድ ርክክብ ተከናወነ  

_______________________________________

በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የኩባ አምባሳደር ሜይሊን ሱዋሬዝ ከስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከክቡር አቶ ወዮ ሮባ እና የግሩፑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሁለቱ አገራት በስኳር ልማት ዘርፍ በጋራ ለመስራት ቀደም ሲል በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ዙሪያ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም በግሩፑ ዋና መስሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተወያዩ፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ወገኖች በምርምርና ልማት ዘርፍ፣ የተለያዩ ምርቶች ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ፣ በፋብሪካና እርሻ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ፣ በሸንኮራ አገዳ ዝርያ ልማት፣ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በባዮቴክኖሎጂና በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በዘርፉ ንግድ በትብብር ለመስራት የሚችሉባቸው መስኮች መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ምርታማነት ማሳደግ፣ በተለይ የባዮቴክኖሎጂ አቅም መገንባት፣ የስኳር ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ በፋብሪካ ጥገናና ኦፕሬሽን አመራር አቅም ማሳደግና የመሳሰሉት ተግባራት እንደሚከናወኑ ነው የሚጠበቀው፡፡

 

በውይይቱ መግቢያ አምባሳደር ሜይሊን በኩባ እና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ በጋራ ለመስራት በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመወያየትና ሁለቱም ወገኖች በጋራ ሊሰሯቸው የተስማሙባቸውን ሥራዎች የማስቀጠል ተልዕኮ ይዘው ወደ ግሩፑ ዋና መስሪያ ቤት መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በበኩላቸው ክብርት አምባሳደሯን ወደ ግሩፑ ዋና መስሪያ ቤት እንኳን በደህና መጡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዙሪያ ኩባ እና ኢትዮጵያ በጋራ እንዲሰሩ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ( ዶ/ር ) እና የኩባው ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር ቫልዴዝ በኩል ቀደም ሲል አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁመው ይህን ተከትሎም የኩባ የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ጋር የጋራ ውይይትና የሥራ ጉብኝት ተደርጎ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አውስተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የኩባ የቴክኒክ ቡድን ከካበተ ልምዱ በመነሳት የአገራችንን የስኳር ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን በሚገባ በመለየት መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉ የቴክኒክ ባለሙያዎች በኩባ በኩል እንዲላክ በግሩፑ በኩል ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎም አምባሳደር ሜይሊን በኩባ የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ የቴክኒክ ቡድን የተላከውንና የአገራችን የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎች ተብለው የተለዩ ጉዳዮችን ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኒክ ቡድኑ መፍትሔዎችን የያዘ ሰነድ ለስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ አስረክበዋል፡፡

የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው የኩባ የስኳር ኢንዱስትሪ የባለሙያዎች ቡድን በስምምነቱ መሰረት ለአገራችን የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የያዘ ሰነድ በመላኩ ምስጋናቸውን ገልጸው ይህም ሁለቱንም ወገኖች ወደቀጣይ ሥራ በቶሎ ለመግባት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከኩባ አቻው አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ መንግስታዊ የስኳር አምራች ኩባንያ ጋር በትብበር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም መፈራረሙ ይታወሳል፡፡