
ፋብሪካው ከአካባቢው አርብቶ አደር ማህበረሰብ ጋር ውይይት አደረገ
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1/3 ስኳር ፋብሪካ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ልማት ፕሮጀክት በሚገኝበት አካባቢ ነዋሪ ከሆኑ የቦዲ ማህረሰብ አባላት ጋር ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጸጥታ እና ደህንነነትን እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ ልማት ሥራውን በተመለከተ ውይይት አደረገ፡፡
በውይይቱ የማህበረሰቡ ባላባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የመስተዳደር አካላት እንዲሁም በፋብሪካው በቋሚነትና በጊዜያዊነት በመስራት ላይ የሚገኙ የማህበረሰቡ ተወላጅ የደህንነትና ጥበቃ፣ የጋራዥ ሠራተኞች እና ኦፕሬተሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1/3 ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ተስፋዬ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ማሳ ውስጥ ከብቶችን ማሰማራትና የአካባቢው የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ ስጋት እየታየበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለእነዚህ ችግሮች የወረዳ መስተዳድር አካላት ከፋብሪካው ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ ያለመስራት፣ በየጊዜው ውይይቶች አለመደረጋቸውና የመሳሰሉት ችግሮች መሆናቸውን መገንዘባቸውን አክለዋል፡፡
አያይዘውም እጅ ለእጅ ተያይዘንና በችግሮቻችን ላይ በመመካከር በየጊዜው መፍትሔ እየሰጠን የአካባቢውን የጸጥታና የደህንነት ሁኔታ እናሻሽላለን፤ የሸንኮራ አገዳ ልማቱን በተጠናከረ መልኩ እናሳልጣለን፤ የስኳር የምርታችንን እናሳድጋለን ለዚህም ከጎናችን እንደምትሆኑ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢው አርብቶ አደር ማሕበረሰብ ባላባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የቀበሌ ሊቀመናብርት እንደዚሁም በፋብሪካ ጽ/ቤቱ በቋሚነትና በጊዜያዊነት በመሥራት ላይ የሚገኙ የቦዲ ማህበረሰብ ተወላጅ የሆኑ የደህንነት ጥበቃ፣ የጋራዥ ሠራተኞች እና ኦፕሬተሮች የፋብሪካው ማኔጅመንት በፋብሪካው በአካባቢው የሚስተዋሉ ችግሮችን በማወያየቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በቀጣይ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ለወንጀል የሚገፋፉና የሚያነሳሱ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም ውይይቶች ችግር ፈቺነት ታምኖባቸው በቀጣይነትና በዘላቂነት የማህበረሰብ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የሳላማጎ ወረዳ መስተዳድርና ፋብሪካው በጋራ ውይይቶችን ቢያመቻቹ ለፋብሪካው ውጤታማነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የውይይቱ ተሳታፊዎች ከብቶቻቸውን በፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ውስጥ ያሰማሩ የማህበረሰቡን አባላት ከፋብሪካው ማሳ እንዲያስወጡ ኃላፊነት ወስደን እንሰራለን፣ ለአካባቢው ጸጥታና ደህንነት ሁላችንም በጋራ ዘብ እንቆማለን በማለት ከስምምነት ደርሰው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡