
“ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ለግሩፑ የሥራ መሪዎች ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው
ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሥራ መሪዎች “ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
የካቲት 25 ቀን 2017ዓ.ም በአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተጀመረውን ስልጠና በንግግር የከፈቱት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያዘጋጀው ይህ ስልጠና በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ሙስናን የሚጸየፍ፣ ታማኝ፣ እንዲሁም አገልጋይ የሆነ አመራር በመፍጠር ረገድ የጎል ሚና አለው ብለዋል፡፡
ስልጠናው ግሩፑ ሙስናን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት እያደረገ ላለው ጥረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ባለፉት ዓመታት ካከናወናቸው የለውጥ ተግባራት መካከል የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል በዋና መስሪያ ቤት እና በፋብሪካዎች በአደረጃጀትና በሰው ኃይል እንዲጠናከር ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የግሩፑ የውስጥ አሠራሮች ብልሹ እንዳይሆኑ መከላከል የሚያስችሉ እና የተጠያቂነት ሥርዓት እየተሻሻለ እንዲሄድ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ከመከናወናቸውንም በላይ በተለዩ ክፍተቶች ላይ ለሥራ መሪውና ሠራተኛው በራስ አቅም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውንም ክቡር አቶ ወዮ አስገንዝበዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታ የግሩፑ የሥራ መሪዎች ከስልጠናው የሚያገኙትን ግንዛቤ በስራ ላይ በማዋል ለተግባራዊነቱ ግንባር ቀደም ሚናቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው መሆኑንም አሳስበዋል፡፡
ከግሩፑ ዋና መስሪያ ቤት፣ ከምርምርና ስልጠና ዘርፍ የተውጣጡ የሥራ መሪዎች እየተሳተፉበትና በቡድን ተከፋፍለው ውይይት እያደረጉበት የሚገኘው ስልጠና ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡